top of page

ጥንታዊውን የላፁ አባ እዮብ ቤተ ክርስትያንን ይተዋወቁ!

  • Writer: Wag Ethiopia
    Wag Ethiopia
  • Nov 23, 2022
  • 3 min read

1) መግቢያ

አስደናቂው ጥንታዊ የኪነ ህንፃ አሻራ፣ ለ1500 አመታት ከፊል ኪነ-ህንጻ የኖረው ላፁ አባ እዮብ ቤተ ክርስትያን! በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በሰቆጣ ወረዳ ሳይታወቅ የኖረ ድንቅ የኪነ-ህንጻ ቤተክርስትያን፤ ኪነ-ህንጻው የዛሬ 1500 አመት ገደማ በአከባቢው በሚገኘው ቁሳቁስ የታነጸ ነው። ታድያ ይህ የሚታየው ኪነ-ህንጻ ለ1500 አመታት ህንጻው በከፊል በዚህ መልክ እንዴት ቆዬ ሲባል ይደንቃል። በርግጥ በዋግ ኽምራ ሰቆጣና በዙሪያው የሚገኙ የህድሞ ቤቶች ለ500 አመታት ድረስ ምንም ሳይፈርሱ እስካሁን አገልግሎት እየሰጡ ስለሚገኙ፣ ይሄው ቤተክርስትያን የዚህን እድሜ መኖሩ ብዙም ላያስደምም ይችል ይሆናል።


2) መገኛ

ይህ ጥንታዊ የህንፃ ቅሪት ከሰቆጣ ከተማ በስተሰሜን አቅጣጫ 20 ኪ/ሜ ርቀት ከተጓዙ ቡኋላ በሰቆጣ ወረዳ የምትገኘውን ማይጉንዶ የተሰኘች ታዳጊ ከተማ ያገኛሉ። ማይ ጎንዶ ከተማ ላይ ከደረሱ በኋላ በስተቀኝ በሚወስደው የእግር መንገድ ይዘው የተወሰነ አቀበቱን ሽቅብ ከውጡ ቡኋላ አግድም በሚወስደው ቀጭን መንገድ ይዘው ይጓዛሉ። ጥንታዊውን የጣሽመነል ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በግራ እየተዉ እጅግ ውብና አስደናቂ የሆነው የጥራሬ ወንዝ ተፋሰስ (Tirari River Basin) ከላይ ወደታች እየተመለከቱ፣ ወንዙን ማዶና ማዶ አቅፎ የያዘው በጥበኛ እጆች የተጠረበ የሚመስለውን የጥራሪን ክንፍ ማየት እንዴት ድንቅ ነገር ነው? በተፈጥሮ እየተደነቁ በግራና በቀኝ በሚገኙ የሳር ጎጆዎች፣ በቅንጭብ አጥር የተሸመጠጡ ቤቶች መካከል አልፈህ፣ አይንህ ተወርውሮ የሚያርፈው ከነዛ ድንቅ የዋግ ኽምራ ተራሮች ነው። ተፈጥሮን እያጣጣምን 9 ኪ.ሜ የሚሆን የእግር ገዞ ካደረግን በኋላ የላፁ አቡነ እዮብ ጥንታዊ ቤተክርስተያን የህንፃ አሻራ አገኘን። ቦታው በምእራብ ጣሽመነል ጊዮርጊስ፣ በሰሜን በለዛ ማርያም፣ በምስራቅ ጥራሪ ወንዝ፣ በደቡብ አኽተራ ማርያም፣ አዋሳኝ ሆኖ፤ ለመታዘብ በሚመስል መልኩ ከሺኽ አመታት በላይ ሳይሰለቻቹ ፊት ለፊት እየተያዩ በሚኖሩት ተስለው የቀመጡ በዋግ ተራሮች ተከቦ ይገኛል። ይህን ድንቅና እድሜ ጠገብ ላጹ ቤተክርስትያንን ከዚህ ቀደም አሚኮ በኽምጣጛ ክፍሉ በፕሮግራም ደረጃ እንደ ተዘገበ ነግረውናል። ታሪክ ነጋሪው ቀሲስ ሊቀ ህሩያን ኃይሌ አለሙ እንደነበሩም ጭምር።


3) ታሪክ

ታሪኩ እንዲህ ነው። በአካባቢው ትውፊትና አሻራ መሰረት የቤተክርስትያኑ ምስረታ 1500 አመታት ወደኋላ ያስጉዘናል፤ ወቅቱ አፄ ካሌብ ኢትዮጵያን ያስተዳድሩ የነበረበት ዘመን ነው፤ ከሰሜን ወደ ደቡብ ክርስትና መስፍፍት ጋር ተያይዞ የተመሰረተ እንደሆነ የአካባቢው ትውፊት አሰረጅ ነው። ከቤተክርስቲያኑ ታሪክ ጋ ተያይዞ የጠየቅናቸው የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ የ93 አመት አዛውንት አቶ ብርሀኑ ክንፉ ሲያስረዱ፣ አባ ሲኖዳ የሚባሉ መናኝ 45 ታቦታት በመያዝ 350 መነኮሳት አሳጅበው በዋግ ኽምራ ምድር ከጥራሪ ወንዝ በስተምእራብ አቅጣጫ "ፃድቃን ጋ" ቃሉ የአገውኛ ሲሆን (የቅዱሳን ዋሻ) ተብሎ በሚጠራ ዋሻ እንደከተሙ ያስረዳሉ፡፡ ይሄውም በአፄ ካሌብ ዘመነ መንግስት እንደሆነም አክለው አስረድተዋል። አቡነ ሲኖዳ ከ45 ታቦታት መካከል አባ እዮብ ለሚባሉ መናኝ ታቦተ ማርያምን አስይዘው "አበ ደረ ማርያም" ፤ "አበ ደረ" በአገውኛ ሲሆን (ኢየሱስ ክርስቶስ) በሚባል ቦታ አሁን ቅሪቱ በሚገኝበት እንዲመሰረትና እንዲያገለግሏት አዘዙ፤ ከዚያም ይህች አስደናቂ የህንፃ ጥበብ ያረፈባት ቤተክርስትያን ተገነባች፡፡ አሁን ላይ በቦታው የሚገኘው የፈረሰ ህንፃ ቤተክርስቲያን ከምስረታው ጋ እኩል እድሜ እንዳለው ይናገረሉ። ይህም ቤተክርስቲያን መካከለኛው ዘመን ላይ የቃጠሎ ጉዳት እንደደረሰበትና ታቦቱም ከቦታው ተነስቶ አኸተራ ማሪያም ወደ ተሰኘ ቦታ እንዲዛወር ተደርጓል።


4) ኪነ-ሕንጻ

ህንፃው ግን እስከዛሬ ታሪክና ሀይማኖት እየተናገረ ከበርካታ መቶ አመታት ቡኋላም ቆሞ ይገኛል፤ እኛም ከልጅነት እስከዛሬ ከዚህ አካባቢ ለቀን አናቅም በማለት ይናገራሉ። የቤተ-ክርስትያኗ የአሰራር ጥበብ አሁን ላይ ከቀረው አሻራ ለማየት እንደሚቻለው ጥንታዊውን የህንፃ አሰራር ጥበብ የሚያሳይ ለየት የለና ድንቅ ነው። ቤተክርስቲያኑ ቅድስት መቅደስ ና ቅኔ ማህሌት ያሉት ነው። አሁን ላይ ከደረሰበት ጉዳት አንፃር ብዙው ክፍል ቢፈራርስም መቅደሱና ቅድስቱ እንዲሁም መንበሩ እርስ በርሳቸው ክብ በሆነ ቅድስት ተያይዘው የተገነቡና ሶስት ዙር ግንባታ ያረፈበት ነው፣በዙሪያው ከአምስት በላይ በሮችና እንዲሁም በርካታ ዝግ (false door)ና ክፍት መስኮቶች ይታያሉ። የተሰራበት ማቴሪያልም በአካባቢው የማይገኝ ከጥራሪ ወንዝ እንደመጣ፣ በተፈጥሮው የተቀረጹ የሚመስሉ አራት መአዘን የሆኑ ነጭ ከለር ባለቸው ጡብ መሳይ አለቶች ነው። የህንፃ ስፋቱንም ስናያው ዛሬ ላይ በዋግ ምድር ከተገነቡ ሰፋፊ ክብ አብያተክርስቲያናት ሁሉ የሰፋ እንደሆነ ያሳያል። ዛሬ ላይ ይህ አካባቢ ኦና ቢሆንም ቅሉ ትላንት ግን የጥራሪ ወንዝን ተከትለው የሰፈሩ ነዋሪዎች እንደነበሩ የሚያሳይ በቤተክርስቲያኑ ዙሪያ የሚገኙ ጥንታዊ የመንደር ፍርስራሾች ማሳያ ናቸው።




5) የቱሪዝም አቅም

የሰቆጣ ወረዳ ባ/ቱሪዝም ፅ/ቤት ኀላፊ ወ/ሮ ደስታ ይሄንን ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ከአካባቢም ስነ ምህዳር ጋ አያይዞ በመጠበቅ በማስተዋወቅ እና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እንሰራለን ይላሉ። ተፈጥሮን የሚያደንቁና ታሪክን የሚጠይቁ የትንግርት ነጋሪዎች ወደ ስፍራው ቢያቀኑ ድንቃድንቅ ትሩፋትን እንደሚያገኙ ግልጽ ነው ይላሉ። እግረ መንዳችንም ሌላኛው ቀልባችን የገዛው ተራራውን መሀል ለመሀል የሚያልፈው የተፈጥሮ ዋሻ ነው ሲሉ ይገልጻሉ ወ/ሮ ደስታ። ይህነን ድንቅ ነገር አስመልክተው የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አቶ መሳይ ፀጋው እንደሚገልጹት፣ አካባቢው ካለው አቀማመጥ ጀምሮ የቤተክርስቲያኑ ህንፃ ቅሪት አሰራርና ለሺኽ አመታት ዝናብ፣ ፀሀይና ቁር እየተፈራረቀበት እንዴት እስከ ዛሬ ሙሉ በሙሉ ሳይፈርስ ለ1500 ዓመታት ዘለቀ ሲሉ እንደ ታሪክ ተመራማሪነታቸው እጅጉን ይደነቃሉ። ይህንንና በአካባቢው የሚገኙ ጥንታዊ መንደሮች ጨምሮ በርካታ ጥናት የሚጠይቅ መሆኑን ገልፀው፣ ቀጣይ የአርኪኦሎጂ ጥናት ቢደረግ አገዎች በዘመኑ የነበራቸውን የአሰራር ጥበብና አኗኗር ለማወቅ ይቻላል፤ ይህ የሚያሳየው ደግሞ የአቑሽም (አክሱም) የአገዎች የጥበብ አሻራ እንደሆነ በጉልህ የሚያሳይ አስረጅ ነው ይላሉ አቶ መሳይ። በመጨረሻም የአካባቢው ኑዋሪዎች ቅርሱ የመላው ኢትዮጵያዊ በመሆኑ እንክብካቤ እንዲደረግለት የጠየቁ ሲሆን የትኛውም ቱሪስት ቢመጣም በደስታ ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።




[ምንጭ: የ Waghimra Communication Facebook ገጽ ፤ ህዳር 13/2015 ዓ.ም]




Comments


Contact Us

Phone:+251-115 549493, Addis Ababa

Phone: +251-334 400424, Sekota

Connect with us
SUBSCRIBE

Thanks for submitting!

WDA is a local CSO registered in Ethiopia (Reg. No. 1855)

© 2023 Wag Technical Advisory Council (WTAC). Proudly created with Wix.com

bottom of page