top of page

How we work

About

Wag Technical Advisory Council (WTAC) was established under the Wag Development Association (WDA) in 2020. WTAC aims to provide a wide ranging technical and professional support to governmental, non-governmental, and private sector stakeholders working in and around Wag Himera. The central role of the WTAC is coordination of efforts by the network of volunteer professionals from all over the world willing to provide technical support to foster sustainable development in Wag Himera. More information is provided below in Amharic.

Open Book

መግቢያ/Introduction

የዋግ አከባቢ እድገት እና ልማት በጊዜ ሂደት የተጠራቀሙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሲፈተን እንደኖረ ለማንም ግልጽ ነው። አከባቢው ለረጅም ጊዜ የተኖረበት እና የታረሰበት፤ ዝናብ አጠር፤ የተፈጥሮ መልክዓምድር አቀማመጡ ተራራማ መሆን እና ቀጠናው ባለፉት ሶስት ክፈለ ዘመናት በተደጋጋሚ የጦርነት እና ግጭቶች ማዕከል ሆኖ መቆየቱ እና የመሳሰሉት የአካባቢው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ስረ መሰረት ናቸው ማለት ይቻላል። ውጤቱም ተደጋጋሚ የድርቅ እና የርሃብ ክስትቶች፤ ስደት፤ ዝቅተኛ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት እና በቂ የተማረ የሰው ሃይል ማፍራት አለመቻል ሆኗል። በአንጻሩ ደግሞ የዋግ አከባቢ ገና ያልተነካ የሚባል ወጣት የሰው ሃብት፤ የተፈጥሮ ሃብት (ማዕድናት፤ ወንዞች፤ የአሳ ሃብት፤ የእንሰሳት ሃብት)፤ የቱሪዝም መስህቦች (የታሪክ፤ የሃይማኖት፤ የባህል እንዲሁም የተፈጥሮ መልክዓምድር)፤ በቀጠናው ለሚደረጉ የንግድ፤ የቱሪዝም እና ማህበራዊ ግንኙትን ለማሳለጥ የሚይረዳ በጎ የማህበራዊ ካፒታል የሚገኙበት አካባቢ ነው። በተለይም ባላፉት ሁለት አስርት አመታት የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች (በቂ ባይሆኑም እንኳ) ነገን የተሻለ ለማድረግ መሰረት ናቸው። ይልቁንም በቅርቡ እያደገ የመጣው የተማረ ወጣት ቁጥር ለአከባቢው እድገት እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው። ሆኖም ግን በአከባቢው ያሉ ጸጋዎችን ለይቶ አለማወቅ፤ አለመጠቀም እና ለመጠቀም ያለው ጉጉት አናሳ መሆንም ከችግሮቹ መገለጫዎች ውስጥ ጎልተው ከሚታዩት ውስጥ ናቸው። ይህም በየዘርፉ የሃሳብ መሪዎችን በማፍራት ረገድ ድክመት እንዳነበረ ያመላክታል። ዛሬ ላይ በደረሰንበት ደረጃ፤ እነዚህን የተጠራቀሙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት የአከባቢው ተወላጅ እና ደጋፊ ባለሙያዎች የተቀናጀ ድጋፍ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ የባለሙያዎቹ አስተዋጾ በተቀናጀ፤ በተማከለ፤ ወጥ እና ተቋማዊ በሆነ መንገድ ቢመራ ተጽእኖ እና አስተዋጾ ዘመን ተሻጋሪ ይሆናል ብለን እናምናለን። ይህም የአከባቢው ልማት በትውልድ ቅብብሎሽ ያለምንም መዛነፍ እንዲመራ እጅግ ይረዳል ብለን እናምናል። በዚህም መሰረት ከአሁን ቀደም ለዋግ ልማት ማህበር (ዋልማ) ተቋማዊ ለውጥ አስፈላጊነትን በተመለከተ ባቀረብነው የመነሻ ሠነድ ላይ የጉባኤ-ማዕምራን (Technical Advisory Council-TAC) የማቋቋም አስፈላጊነት ማንሳታችን ይታወሳል። የጉባኤ-ማዕምራኑ መመስረት በዋግ አካባቢ ፀጋዎች እና እሴቶች ላይ ጥናት እና ምርምር የማድረግ ዝንባሌን በማሳደግ የበጎ ፈቃድ ጥናት እና ምርምር ባህል እንዲሆን ይረዳል ብለን እናምናለን።

የጉባኤው ስራዎች የጽንስ ሃሳብ መሰረት/Theoretical Foundation

የጉባኤው ራእይ የዋግ አካባቢ ዘላቂ ልማት እውን ሆኖ ማየት ነው። ስለሆነም፤ በማዕምራን ጉባኤ የሚሰሩ ስራዎች በሙሉ የዋግን ዘላቂ ልማት ለማረጋጋጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚረዱ ናቸው። በመሆኑም፤ በጉባኤው አስተባባሪነት የሚሰሩ ስራዎች በሙሉ በዘላቂ ልማት ጽንስ ሃሳብ ማዕቀፍ የሚታዩ እና የሚመሩ ናቸው። በዘላቂ ልማት ጽንስ ሃሳብ መሰረት (the concept of sustainable development) አንድ አከባቢ አራት የሃብት ምሶሶዎች አሉት። እነዚህም፤ 
 

  1. የሰው ሃብት /Human Capital/ ፦ የሰው ሃብት የተማረ እና ጤናማ ሕብረትሰብን ያሳያል። ስለሆነም፤ የሰው ሃብት ልማት በዋናነት የትምህርት እና የጤና አገልግሎት መስፋፋት ይጠይቃል። ከትምህርት እና ጤና ጋር የተያየዙ ስራዎች በሙሉ መዳራሻቸው የሰው ሃብት ልማትን ማፋጠን ነው።

  2. የቁስ ሃብት /Physical or Reproducible or Manmade Capital/ ፦ የቁስ ሃብት በዘመናት ሂደት የተሰሩ ቤቶችን፤ የፈሩ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ የመንግስት እና የግል ወረቶችን፤ መሰረተ-ልማቶችን ያመላክታል። በመሆኑም የቁሳዊ ሃብቶች በከተሞች መስፋፋት፤ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፤ በቁጠባ እና በነፍስ ወከፍ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ወረቶች መጠንይለካል። በተለምዶም፤ የቁስ ሃብት የአንድ ማህብረሰብ የስልጣኔ እና የእድገት ማሳያ ተደረጎ ይወሰዳል።  

  3. የተፈጥሮ ሃብት /Natural Capital/ ፦ የተፈጥሮ ሃብት የትኛውንም የኢኮኖሚ ጥቅም ያለው ወይም የተፈጥሮ ስነ-ምህዳር ሚዛናዊነት የሚያስጠብቅ በተፈጥሮ የተሰጡ ጸጋዎችን (ለምሳሌ፦ ተራራሮች፤ ውሃ፤ አፈር፤ አየር ንብረት፤ ማእድናት፤ ደን፤ አሳ) ያጠቃልላል። 

  4. የማህበራዊ ሃብት /Social Capital/ ፦ የማህበራዊ ሃብት በአንድ ማህብረሰብ ውስጥ ያለውን የእርስ በእርስ መስተጋብር፤ መተማመን እና የመተጋገዝ ልምዶች እና እሴቶች ከፍ ሲልም በመንግስት እና በህብረተሰብ መካካል ያለውን መተማመን እና ግንኙነትን ያቅፋል። የማህበራዊ ሃብት ብዙን ጊዜ በአንድ አከባቢ የታሪክ፤ የባህል እና የሃይማኖት እሴቶች መስተጋብር የሚፈጠር፤ በእነሱም ተጽዕኖ ስር የሚሆን እና የሚገለጥም ጭምር ነው። ማህበራዊ እሴቶች እና ልምዶች በትውልዶች መካከል ያለን ግንኙነት ይቀርጻል። 

 

 

ከላይ ያየናቸው የዘላቂ ልማት የሃብት ምሶሶዎች በተለያዩ ባለድርሻ አካላት (በአከባቢው ህብረተሰብ፤ በየደረጃው ባሉ የመንግስት አካላት፤ የግል-ዘርፍ፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና አለምዓቀፍ ተቋማት) ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ ስራዎች፤ ተሳትፎ እና ድጋፍ ይፈራሉ፤ ይስፋፍሉ፤ ይዳብራሉ ወይም ይጠበቃሉ። የዋግ ልማት ማህበር (ዋልማ) የማዕምራን ጉባኤ እና በስሩ የሚዋቀረው ድረ-ማዕምራን ዋና ስራም የሚሰራቸው ስራዎችን ከላይ በየተጠቀሱት ባለድርሻ አካላት ለሚሰሩ ስራዎች ግብዓት፤ አጋዥ እና መሪ የሚሆኑ የጥናት እና ምርምር እና የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰነዶችን እና መረጃዎችን መሰነድ፤ ማዘጋጀት እና መተንተን ነው። 

   አስፈላጊነት/Rationale

የዋልማ ጉባኤ-ማዕምራን ማቋቋም ያስፈለገበት ዋና ምክንያት የአከባቢውን ዘረፈ ብዙ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና መዋቅራዊ ችግሮች የአከባቢውን የተፈጥሮ፤ የማህበራዊ፤ የሰው እና ቁሳዊ ሃብቶችን በመጠቀም የዋግ አከባቢን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ እንዲቻል በሁሉም የሙያ ዘርፎች የተሰማሩ የአከባቢውን ተወላጅ እና ደጋፊ ባለሙያዎች የሚሰባሰቡበት መድረክ ለመፍጠር ነው። በተጨማሪም፤ በአከባቢው ለሚደረጉ ማናቸውም የልማት እቅዶች እና ስራዎች አጋዥ እና ማጣቃሻ የሚሆን ወጥ የሆነ የመረጃ እና የእውቀት መፍጠሪያ የልሕቀት ማዕከል ለማደርጀት ነው። 

    ተልዕኮ/Mission 

የዋግ ልማት ማህበር ጉባኤ-ማዕምራን ዋና ተልዕኮ በሰው ሃብት፤ በቁሳዊ ሃብት፤ በተፈጥሮ ሃብት፤ እና በማህበራዊ ሃብት ልማት ዙሪያ ለሚደረጉ እንቅስቃሴች ደጋፊ የሚሆኑ የጥናት እና ምርምር መረጃዎች በማዘጋጀት፤ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት፤ የአዳጊ ወጣቶችን የበጎ ፈቃደኝነት ፍላጎትን እና የስራ ባህልን በማሳደግ፤ በዋግ አከባቢ ጥናት እና ምርምር የማድረግ ዝንባሌያቸውን በማሳደግ፤ እና ከዓለም ሃገራት ወይም ክፈለ ሃገራት ለዋግ እድገት አርዓያ የሚሆኑ ማህበረሰቦችን በመምረጥ የዋግ ዘላቂ ልማትን መቃኘት እና መደገፍ ነው። 

Mountain Ridge
Goals2.png

ዓላማዎች/Objectives

  • በዋግ አከባቢ ለሚሰሩ የመንግስት፤ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፤ የሲቪክ ማህበራት እና የግል ዘርፉ የልማት እንቅስቃሴዎችን የሚያግዙ ጥናታዊ ጽሁፎችን ማዘጋጀት እና የፕሮጀክት ፕሮፖዛሎችን መቅረጽ (ወይም ቀረጻዎች ላይ መሳተፍ)

  • በዋግ አከባቢ ለሚደረጉ ሳይንሳዊ ጥናት እና ምርምሮች፤ የፌደራል እና የክልል መንግስታት ጥናቶች ላይ የባለሙያ አስተያየት እና ትንታኔ መስጠት

  • የዋግ አከባቢን ማህበራዊ፤ ታሪካዊ፤ ባህላዊ፤ ቁሳዊ፤ እና ተፈጥሯዊ ሃብቶችን በየጊዜው መሰነድ እና የመረጃ ቋት ማዘጋጀት

  • በዋግ አከባቢ የሚሰሩ የልማት ስራዎች እና እቅዶች ከአለም-ዓቀፍ፤ ከአገር-ዓቀፍ እና ክልል-ዓቀፍ አቅጣጫዎች እና ሂደቶች ጋር እንዲዛመዱ እና ተመጋጋቢ እንዲሆኑ ማስቻል

  • በዋግ አከባቢ የሚሰሩ የልማት ስራዎች እና እቅዶች ከአከባቢው የቆዩ እና ልማዳዊ እውቀቶች እና ዘዴዎች ጋር ተጣጥመው እንዲሄዱ ማመቻቸት

  • በዋግ አከባቢ የሚሰሩ የልማት ስራዎች እና እቅዶች ለመደገፍ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ማዘጋጀት እና ማመቻቸት

  • የዋግ አከባቢን ልማት በዘላቂነት ለመደገፍ እንዲቻል የታዳጊዎች እና ወጣቶች የበጎ ፈቃደኝነት እና ስራ ባህልን ለማሳደግ ማመቻቸት  

  • የዋግ ልማት ማህበር ስራዎችን ለመደገፍ የሚሆኑ አነስተኛ ፕሮጀክቶችን (easily fundable & accessible projects) በተከታታይ እየቀረጹ ማስቀመጥ

  • የዋግ ልማት አቅጣጫን ለመቃኘት አጋዥ ይሆን ዘንድ፤ ከዓለም ማህበረሰብ ውስጥ በየልማት ዘርፉ አርዓያ የሚሆኑ አከባቢዎችን መምረጥ እና ልምዳቸውን መቀመር

ግቦች/Goals

  • የዋግ የሰው፤ የቁሳዊ፤ የተፈጥሮ፤ እና የማህበራዊ ሃብት መሰረቶች አሁን ያሉበትን ደረጃ፤ ለወደፊቱም እድሎች እና ተግዳሮቶች መለየት እና መተንተን 

  • የዋግ የሰው ሃብት፤ የቁሳዊ ሃብት፤ የተፈጥሮ ሃብት፤ እና የማህበራዊ ሃብት ልማት አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ መለየት እና መተንተን

  • የዋግ የሰው ሃብት፤ የቁሳዊ ሃብት፤ የተፈጥሮ ሃብት፤ እና የማህበራዊ ሃብት ልማትን ለማፋጠን ሊወሰዱ ስለሚገቡ ስራዎች (intervention options) መለየት እና መተንተን

  • በዋግ አከባቢ የተፈጥሮ ሃብት፤ የምጣኔ ሃብት፤ የባህል እና የታሪክ እምነቶች፤ ልምዶች እና እሴቶች (beliefs, norms, and values) ላይ የጥናት እና ምርምር የሚደደርግ ዘላቂ የሆነ የምርምር ትሥሥር (Research Network) መፍጠር

ተግባር እና ሃላፊነት/Duties & Responsibilities 

  • የጥናት እና ምርምር ሰነዶች ማዘጋጅት እና ማሰራጨት

  • የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ማዘጋጀት እና እንዲሰጡ ማመቻቸት

  • ለዋግ ልማት ማህበር እና ሌሎች የልማት ድርጅቶች የፕሮጀክት ምክረ ሃሳቦችን ማበልጸግ

  • ለዋግ ልማት ማህበር አነስተኛ የፕሮጀክት ሰነዶች እያዘጋጁ ማስቀመ

  • በቀጠናው ልማት ዙሪያ ሙያዊ ትንታኔዎች እና አስተያየቶችን ማቅረብ

የማስፈጸሚያ ስልቶች/ Delivering Mechanisms 

የማዕምራን ጉባኤ የተለመዱትን የእውቀት አስተዳድር ስልቶችን (Knowledge Management Strategies) በመጠቀም ስራዎችን ያከናውናል፤ የስራ ውጤቶችንም ያሰራጫል። ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹ ፦

 

  • የጥናት እና ምርምር ውጤቶች በማሳተም እና በማሰራጨት

  • ስልጠናዎች፤ ወርክሾፖች እና ሴሚናዎች በማዘጋጀት

  • የስትራቴጂክ ሰነዶች በማዘጋጀት

  • የሪፖርት ሰነዶች በማዘጋጀት

  • የመረጃ ቋት (database) በማዘጋጀት

  • መጻሕፍት መጻፍ፤ ቃለ መጠይቆች እና የሚዲያ ትንተናዎች ላይ በመሳተፍ

  • ከሃገር ውጭም እና ውስጥ (በተለይም በቀጠናው ካሉ) ዩኒቨርሲቲዎች፤ የእርሻ ምርምር ማዕከላት ጋር በትብብር በመስራት

Services.png

ከጉባኤው ከሚጠበቁ የስራ ውጤቶች ተጠቃሚዎች (Beneficiaries of the Deliverables) 

ጉባኤውን ተቋማዊ ለማድረግ በዋልማ ስር ማዋቀር አስፈለገ እንጂ አገልግሎቱ እና ተደራሽነቱ ለሁሉም የአካባቢው ልማት ባለድርሻ አካላት ማለትም:

 

  • የዋግ ልማት ማህበር (ለፖሊሲ እና ስትራቴጂ እና ፕሮጀክት/ፕሮግራም ቀረጻ እና እቅድ ለማዘጋጀት) 

  • ለግሉ ክፈለ-ኢኮኖሚ (የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማጥናት እና ለማሳየት)

  • ለመንግስት አካላት (የአስተዳዳር እና ልማት ስራዎች  ለማቀድ እና ለመገምገም)

  • ለመንግስታዊ ላልሆኑ ግብረሰናይ ድርጅቶች እና የሲቪክ ማህበራት (ለማቀድ፤ የእርዳታ ድጋፍ ለማሰባሰብ)

  • ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች (እንደ አስፈላጊነቱ እና አግባቡ)

የጉባኤው የአሰራር ሂደት/Operational Management 

ጉባኤው ከየትኛውም የህብረትሰብ ክፍሎች እና የልማት ባለድረሻ አካላት የሚመጡ ጥያቄዎችን፤ የመነሻ ሃሰቦችን እና ጥቆማዎችን ይቀበላል። ይህም ማለት ከግለሰቦች (በግል ወይም በቡድን)፤ ከድረ-ማዕምራን (በግል ወይም በቡድን ተነሳሽነት)፤ ከግሉ ክፍለ-ኢኮኖሚ፤ ከመንግስት አካላት፤ እንዲሁም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች መነሻ ሃሳብ፤ ጥቆማ፤ እንዲሁም ፋላጎት ለማዕምራን ጉባኤ ሊቀርብ ይችላል።

 

ለተዘክሮ (for the sake of credit & documentation) እና ለተጣያቂነት (transparency & accountability) ሲባል ጥያቄው ወይም ጥቆማው በጽሁፍ ቢቀርብ ይመከራል። የማዕምራን ጉባኤም የመጣውን ጥያቄ መርምሮ (ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን እና ባለው የሰው እና ገንዘብ ሃብት ሊሰራ የሚችል መሆኑን ገምግሞ) ለድረ-ማዕምራን መረጃ ያደርሳል።

 

ጉባኤው ከሚያገኛቸው የፈቃደኘነት መልስ፤ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ባለሙያዎች መስራት እንፈልጋለን ብለው በአባልነት ቅጽ ላይ ባስቀመጡት መሰረት ለመጣው ጥያቄ አግባብነት ያለው ልምድ (background & experience) አላቸው የሚላቸውን ባለሙያዎች መርጦ የስራ ቡድን ያዋቅራል። የስራ ቡድኑ የቡድን (ወይም የፕሮጀክት) አስተባባሪ ይኖረዋል። ይህ የስራ ቡድን የቀረበውን ጥያቄ/ሃሳብ ወደ ፕሮጀክት ቀይሮ፤ የሚያስፈልጉ የሰው እና ቁሳቁስ ግብአቶችን፤ የሚወስደውን ጊዜ፤ ለስራው የሚያስፈልጉ የመንግስት ወይም መ.ያ.ድ አጋሮችን እንዲሁም ሃሳቡ ቢተገበር ፈጻሚ የሚሆነውን አካል (Implementing Agency) እና የመጨረሻ ተጠቃሚ የሚሆነውን (end user or ultimate beneficiary) ገልጾ ለማዕምራን ጉባኤ ይሳውቃል። የማዕምራን ጉባኤውም ይህንን ለጉባኤው የዋልማ ጽ/ቤት ተጠሪ (TAC Focal Person) እና ለተለዩት የፕሮጀክት አጋር (Project Partners) አካላት ያሳውቃል። ር

የጉባኤ-ማዕምራን አባላት/Technical Advisors Council

የጉባኤ-ማዕምራን ----- አባላት ይኖሩታል። አባላቱ በተለያየ የሙያ ዘርፍ ልምድ ያካበቱ ቢሆን ይመረጣል። የአባላቱ ስብጥር በተቻለ መጠን፤ የጾታ፤ የእድሜ፤ የማህብረሰብ እና ትምህርት ዝግጅት እና ልምድ ብዝሃነት የሚሳይ ቢሆን ይመረጣል። የጉባኤው አባላት በየ ----- አመቱ ይቀየራሉ። ለጉባኤው የሚሆኑ አባላት ከድረ-ማዕምራን አባላቱ ----- ጥቆማ ተደርጎ የዋልማ ስራ አመራር ቦርድ ይሁኝታ ያገኙ ------ አባላት ይጸድቃሉ። የጉባኤው አባላት ደግመው የመመረጥ እድል አላቸው። የአሰራር ልምዶችን ለማሸጋገር ያመች ዘንድ የስራ ዘመናቸውን የጨረሱ አባላት እንደ ክብር አባላት (honorary members) ሆነው መሳተፍ ይችላሉ። 

የድረ-ማዕምራን አባላት / Network of Professionals

የድረ-ማዕምራን (ዘዋግ!) አባላት የዋግ ተወላጅ እና ልማት ደጋፊ በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎች ስብስብ (resource pool) ነው። ባለሙያዎቹ በተለያየ የስራ መስክ፤ በአገር ውስጥ እና ውጭ የሚኖሩ ናቸው። ድረ-ማዕምራን ሁለት ዋና ዋና ተግባራት አሉት። አንደኛው፤ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የዋግ ልማትን በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች እና ጥቆማዎች ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ተንትኖ የሪፖርት እና የስትራቴጂክ ሰነዶችን አዘጋጅቶ ማቅረብ ነው። ሁለተኛው፤ ለዋግ ልማት ይጠቅማሉ በሚሏቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በግል ወይም በቡድን ጽሁፎችን ማዘጋጀት፤ ሲሚናሮችን ማድረግ፤ ስልጠናዎችን መስጠት እና ንግግሮችን (public lectures) ማድረግ ነው። በአጠቃላይ ዋግን በተመለከተ ተጣያቂ እና መካሪ የሚሆን የበጎ ፈቃደኛ ማዕምራን (technical & professional persons) ስብስብ ነው።

Contact Us

Phone:+251-115 549493, Addis Ababa

Phone: +251-334 400424, Sekota

Connect with us
SUBSCRIBE

Thanks for submitting!

WDA is a local CSO registered in Ethiopia (Reg. No. 1855)

© 2023 Wag Technical Advisory Council (WTAC). Proudly created with Wix.com

bottom of page